ዜና

ጎንደር በ10 ሚሊዮን ብር የዳግማዊ ቴዎድሮስ መታሰቢያ ማዕከል ልትገነባ ነው

ሙዚየም፣ ቤተ መጻሕፍት፣ ትምህርት ቤትና ሌሎች የአገልግሎት መስጫ ክፍሎች ያሉት ማዕከሉን ለመገንባት 10 ሚሊዮን ብር ይፈጃል፡፡ የማዕከሉን ዲዛይን አልትሜት ፕላን የተባለ ተቋም በነፃ ሠርቶ አበርክቷል፡፡

የመሠረት ድንጋዩን ያኖሩት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር በረከት ስምዖንና የገቢዎች ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር መላኩ ፈንቴ ናቸው፡፡ በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ሊቀ ትጉሃን አስታጥቄ አባተ እንደ አፄ ቴዎድሮስ ሁሉ ሌሎች ጀግኖች የሚታሰቡበትና የሚዘከሩበት ተግባር ሊከናወን ይገባል ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል “ኢትዮጵያን በጎንደር” ፌስቲቫል አጋጣሚ በተዘጋጀው መድረክ ላይ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ሰይድ እንደተናገሩት፣ በክልሉ ላለፉት ዓመታት የቱሪስት ፍሰቱ 30 በመቶ አድጓል፡፡ አምና ከ315 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱንና ጎንደር ከተማና ዙርያዋን (ሰሜን ጎንደር ዞን) ከጎበኙ የውጭና የአገር ውስጥ ቱሪስቶችም ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መግባቱንም ተናግረዋል፡፡